;

የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ - ከፊውዳል አርስቶክራሲ እስከ አብዮታዊ ዲሞክራሲ

Published March 15, 2024, 4:01 p.m. by FNN

1026የመጀመሪያ እትም መግቢያ

የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በሚለዉ ርዕስ ላይ ለመፃፍ አስቤ የነበረዉ ከአዲስ አበባ ዩኒቬርስቲ የፖለቲካል ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ድግሪዬ ማሟያ ከተፃፈዉ ጽሑፍ ጊዜ ጀምሮ ነዉ፡፡ በዚያን ወቅት አማካሪዬ የነበሩት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ ይህ አርእስት ለመጀመሪያ ድግሪ ማሟያ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በስፋት ሊፃፍበትም የሚችል መሆኑን እንደምክርም እንደአስተያየትም በቃል ጣል አድርገዉልኝ የነበረዉን መሠረት በማድረግ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለመፃፍ ያደረብኝ ሐሳብ ከውስጤ ሳይጠፋ ቆይቶ የነበር ቢሆንም፤ ያጋጠሙኝ የሕይወት ውጣ ውረዶች እንኳን ጽሑፍ ማዘጋጀት ቀርቶ በሕይወት መኖር ራሱ ጥያቄ ምልክት ዉስጥ አስገብቶኝ ስለነበር ቅድሚያ አልተሰጠውም፡፡ በተለይ በደርግ መውደቂያ አከባቢ የነበሩ ሁኔታዎችና ቆይቶም ከ2001 እስከ መጋቢት 2002 ድረስ ለፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ስሰራ በነበረበት ጊዜያቶች የነበሩ ሁኔታዎች ለግል ሕይወቴ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቤ ጭምር እጅግ አሳሳቢና አስጨናቂ ነበሩ፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ መሀከል ባሉት ጊዜያት ለዚህ አርእስት የሚሆኑ ጽሑፎችና ሰነዶችን ከማሰባሰብና ከማንበብ አልተቆጠብኩም ነበር፡፡

አንዳንድ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እንደሚሉት በያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ ቢያንስ አንድ መደብል የሚሆንና የሚፃፍበት አርእስተ ጉዳይ አይጠፋም የሚሉት ነገር፤ እኔም ዉስጥ ይኖር ይሆን? ብዬ ማሰብ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ መቆየቱ ጠቅሞኝም ጎድቶኝም ሊሆን ይችላል፡፡ የጠቀመኝ ብዙ ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብና ለማንበብ በመቻሌ ሲሆን፤ የጎዳኝ ደግሞ አንዳንዶች ተያያዥ ጉዳዮችን ረስቻቸዋለሁ፣ አንዳንዶች ደግሞ ጊዜ ያልፉባቸዉና የዛሬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ የዕድገት ደረጃ በእርግጥ በዓይነት እንኳን ባይሆን የመጠን ልዩነት በስፋት የሚታይበት ስለሆነ እንድጥላቸዉ ወይም እንድተዋቸዉ አስገድደውኛል፡፡

የኢትዮጵያን የፓርቲ ፖለቲካ ጉዳይ ለመፃፍ ከየት ጊዜ መጀመር ይሻላል 

 

ብዬ ላሰብኩት ሁኔታ ከአፄ ኃይሌ ሥላሴ የአገዛዝ ዘመን መነሳት በቂ እንደሚሆን ግንዛቤ አድርጌአለሁ፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲ ነባራዊ ሁኔታዎች ማቆጥቆጣ የጀመሩት በዚሁ ጊዜ ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካል መመሰቃቀል የጀመረዉ ከአፄ ቴዎድሮስ አገዛዝ ጀምሮ (ከዚያ ቀደም ያለ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም) ስለሆነ፤ በውስን ደረጃም ቢሆን ያንን ቢያጠቃልል ከተነሳሁበት ዓላማ አንፃር ምሉዕ ያደርግልኛል ብዬ ስላሰብኩ፤ ከዚያዉ እንዲሆን አድርጌአለሁ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ፓርቲ ፖለቲካ ጽሑፌ የቴዎድሮስ፣ የዮሐንስ፣ የምኒልክ፣ የኃይሌ ሥላሴ ማለትም ፊዉዳል አርስቶክራሲ ባልኩትና፣ እንዲሁም የደርግና የሕወሓት አገዛዞች ማለትም አብዮታዊያንን በሚወክል መልክ ተከፋፍሎም፣ ተደበላልቆም ቀርቧል፡፡ የአጭር ጊዜም ቢሆኑ በመሀል የሚገኙ አገዛዞችም (ተክለ ጊዮርግስና እያሱ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ የየራሳቸዉ አሻራ ስለነበራቸዉ በቆዩበት የጊዜ መጠንና ለማከናወን በሞከሩት ሥራ አንፃር እንዲታከሉበት ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር አንድ ሊታወቅ የሚገባ ነገር አለ፡፡ ብዙ ሊፃፍበት የሚችል የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በኔ አነስተኛ ሙከራ ጅምር ቢሆን እንጂ ብዙ ሊታወቁና ሊፈተሹ የሚገቡ ጉዳዮች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡

ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች፤ አርስቶክራሲና አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ ዋናዉን የመጽሐፉን አርእስት አፅንዖት ለመስጠት ተቀምጠዋል፡፡ ሁለቱም የአገዛዝ ሥርአቶች መሆናቸው ግንዛቤ ተወስዶ በግርድፉም ቢሆን የእነዚህ ሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች ትርጉም ማግኘት ለተነሳሁበት የመጽሐፉ ይዘት ተፈላጊዉን ነገር ያላብሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመዝገበ ቃላት ትርጉም መሠረት አርስቶክራሲ በሕብረተሰብ ዉስጥ ከፍተኛዉን ሥፍራ የያዘ ሰዉ ወይም የያዙ ሰዎች አገዛዝ ነዉ፡፡ በጁሃሪ (ገጽ 421) ሥራ ዉስጥ ቦል የሚባል ፀሐፊ እንደሚለዉ አርስተክራሲ የሚባለዉ ሥርአት የፖለቲካ መሪዎቹ ራሳቸዉን ከሥልጣን ምንጭ ከሆነዉ ሕዝብ በላይ አድርገዉ የሚያስቀምጡበት፣ የፖለቲካ ክብርና ተቀባይነትን በኃይል በማስገደድ ለማስጠበቅ የሚሰሩበት የፖለቲካ ሥርአት ነዉ እንዳለው ሁሉ፤ በዚህ ጽሑፍም ተገቢ ቦታዉ ላይ እንደሰፈረዉ ሁሉ አብዮታዊ ዲሞክራሲም ከዚሁ ያልተለየ መሆኑን ለማየት ስለምንችል v

 

አርስቶክራሲና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የቅርፅ ቢሆን እንጂ የይዘት ልዩነት እንደሌላቸዉ ያስገነዝብልኛል ብዬ አምናለሁ፡፡

በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ፓርቲ ፖለቲካ ዉስጥ የዉጪ ኃይሎች ሚናም ቀላል እንዳልነበር ስለሚታወቅ፤ ቀንጨብ አድርጌ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የሱዳን፣ የሱማሊያና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወይም የአፍሪካ ሕብረት እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኤርትራ ተፅዕኖ ምን እንደሚመስል አንስቻለሁ፡፡ በመጨረሻም ጥሩነህ ገምታ ማነዉ የሚለዉን ትንሽ ለማስጨበጥ የተወሰኑ ገፆችን አክዬበታለሁ፡፡ ከፖለቲካ ተሳትፎ አንፃር የ60ዎቹ በብዙ መልኩ ቢቀድሙኝም፤ የ70ዎቹ እንቅስቀሴ ዉስጥ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ያጋጣሚ ነገር ሆኖ ብዙ ተሳትፎዬ ከተቃዉሞ ጎራ ስለሆነ፤ ከሞትና እስር በመለስ የሕይወት መመሰቃቀል አጋጥሞኛል፡፡ እዚህ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተለይም እምቦቆቅላ ሕፃናት ከወላጆቻቸዉ ጉያ እየተወሰዱ ወይም የወላጆቻቸዉ ዓይን እያየ በተገደሉበት አገር ዉስጥ፤ በእኔ ላይ እንግልት ደርሷል ብዬ ለማጉላት ሳይሆን፤ ስለአንድ ነገር የሚፅፍ ሰዉ የጀርባ ታሪኩ ምን እንደሚመስል ቢታወቅ፤ ካልታሰበ ስህተት ይገላግላል ብዬ ነዉ እንጂ፤ ለመንገላታትማ ከኔ የበለጠ የተንገላቱ ሰዎች እንደነበሩና ዛሬም እንዳሉ አጥቼ አይደለም፡፡ ከፍ ሲልም ሕይወታቸዉን መስዋዕት ያደረጉም ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ሳይታወቀኝ ቀርቶ አይደለም፡፡

ይህ የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ጽሑፍ የተዘጋጀዉ በአብዛኛዉ ቀደም ሲል በተፃፉ መረጃዎች (በእንገሊዘኛው ሰከንደሪ ሶርስ በሚባል) ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡ ከቋንቋም አንፃር የሦስት ቋንቋዎች የአማርኛ፣ እንግሊዘኛ እና አፋን ኦሮሞ ድብልቅ ነዉ፡፡ እንዲያዉ ተዛማጅ ናቸዉ ካልኳቸዉና የመተርጎም አቅም ካልፈቀደልኝ በስተቀር ሳልተረጉማቸዉ እንዳሉ በጥሬያቸዉ ተጠቅመባቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድም የትርጉም ሥራ የራሱ ዲስፒልን የሚፈልግ ሲሆን፤ ሌላዉ የበለጠ ትኩረቴን የሳበዉ አንባቢዎቼ ኦሪጅናሉንና ዋቢ ያደረኩዋቸዉን ጽሑፎች በትርጉም ሥራ ሂደት ዉስጥ ሳይዛቡ ባሉበት ሁኔታ እንዲያገኙና ፍርዳቸዉን እንዲሰጡኝ በማለት በዚህ ድጋሚ ሕትመትም በነበሩበት vi

 

ሁኔታ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ጽሑፍ የፓርቲ ፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ ከወገንተኝነት ነፃ ሆኜ ጽፌአለሁ የሚል መመፃደቅ እንዳልዳዳኝ ለአንባቢዎቼ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ የዚህ ዓለም፤ በተለይም በዘር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በኤኮኖሚ፣ ወዘተ በተከፋፈለ ኢትዮጵያ አገር ዉስጥ ሕይወቴን ያሳለፍኩ ኢትዮጵያዊ ሰዉ ስለሆንኩ፤ ብዙ ሰዎች እንደሚያረጉት እኔም የራሴን አቋም አካትቻለሁ፡፡ የአካዳሚ ሥራ ከሚሰሩ በስተቀር (እነሱም አንዳንዴ አያደርጉትም አይባልም) ያንን የማያደርግ ሰዉ ደግሞ የለም፡፡ የዜጎችን ማንነት የሚሸረሽሩ ሁኔታዎች የመኖራቸዉን ያህል ገንቢ አስተሳሰብ የሆኑም ሐሳቦች ብዙ ናቸዉ፡፡ ገንቢ የሚባለዉን አስተሳሰብ ለመቀላቀል ሲባል በኢትዮጵያዊያን መሀከል አይነኬ ይባሉ የነበሩትን የዘርና የሃይማኖት ነገሮች ነካክቻለሁ፡፡ ለምሳሌም ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን አበሻ ማለት ምን ያህል ይጥማል ወይም አይጥምም የሚለዉን ሰዎቻችን እንዲነጋገሩበት፤ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ተመስርቶም በኢትዮጵያዊያን መሀከል ሲታዩ የነበሩ መበላለጥን አስመልክቶ ለመግለፅ የፈለኩት፤ በሕዝቦች መሀከል ጥላቻን ለመቆርቆስ ሳይሆን በሽታችንን ከገለፅን በርግጠኛነት መድኃኒት ማግኘት ይቻላል ብዬ አስቤ ነዉ፡፡ ወይም ፖለቲከኞች እንደሚሉት ችግራችንን መግለጽ ከቻልን ለመፍትኼዉ ግማሽ መንገድ እንደተጓዝን ይቆጠራል ለማለት ፈልጌ ነዉ፡፡ ወይም መጥፎ ሰዎች እንዳያሸንፉ ጥሩ ሰዎች እጃቸውን አጥጠፈው መቀመጥ የለባቸውም የሚባለውን የአዋቂዎች ብህል ለማሳየት ፈልጌ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ይህንን መጽሐፍ በስሜት ተነሳስቼ የፃፍኩ ባይሆንም የተሳሳትኩ ነገር እንደሚኖር አልጠራጠርም፡፡ በሰዉ ሥራ ዉስጥ መሳሳት ቢኖርም ትልቁ ነገር መሆን ያለበት ስህተትን በአስተዉሎት ተቀብሎ አለመስተካከል መሆኑ ሊሰምርበት ይገባል፡፡ ይህ መጽሐፍ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተከሰተዉ የፓርቲ ፖለቲካም ሆነ አመራር ችግሮች መፍትኼ ለማፈላለግ ለምን ብሎ ራሱን ለሚጠይቅ ሰዉ መልሱን ለማግኘት የበኩሉን መነሻ ሐሳብ ሊያመነጭ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም በክብር የሚቀበሉልኝ የመኖራቸዉን ያህል የሚከፉብኝ እንደሚኖሩ በእርግጠኛነት እጠብቃለሁ፡፡ vii

 

በፓርቲ ፖለቲካ ጉዳዮቻችን የሚገቡ የሩቅና የቅርብ ኃይሎች ምን ያህል ጠቀሙን? ምንስ ያህል ጎዱን? ተገቢ መልስ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለድክመታችን፣ ስለኋላቀርነታችን፣ ስለሰፊ ልዩነታችን፣ ፖለቲካን ከቅመኝነትና ከጠላትነት አመለካከት ባሻገር ምን ያህል ጣታችንን ወደራሳችን ቀስረናል? መልስ መስጠት ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ሳይሆን እጅግ አልፎን ሄዷል፡፡ ልንደርስበት የምንችል ቢሆንም የሚያስከፍለን ዋጋ ግን ትልቅ ነዉ፤ የአገራችንን አንድነት እስከ መፈታተን ሊደርስ በሚችል ደረጃ ማለት ነው፡፡ በዉሸት ዲሞክራሲና በዉሸት ዕድገት መኮፈሱን ትተን እራሳችንን መመገብ ባለመቻላችን እፍረት ሳይሰማን፤ በዓለም ሕብረተሰብ ፊት ለመቆም መቻላችን ወይም መገደዳችንን ሁለንትናችንን መፈተሽ እንዳለብን ሁሉ፤ አሁን ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር ሕዝባችሁን መምራት አልቻላችሁም እስኪንባል ድረስ መጠበቁ እንዴት እንደሚያሸማቅቅ ማሰቡም አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ብንባልም ነገሩ ትክክል በመሆኑ ይህንን ገልፆ መፃፍ ደግሞ ከራስ ጋር ትግል ማድረግ ይጠበቃል ለማለት የመጀመሪያ ሰዉ ባልሆንም እኔም የበኩሌን አስተዋጽኦ እንዳደረኩ ይቆጠርልኝ አላለሁ፡፡

በመጨረሻም፤ የኢትዮጵያ ገዥዎች ለሠሩት ወንጀል ክህደት ዓመላቸው እንደሆነ ግንዛቤ ተወስዶ፤ የነበርኩበት ሥርአት ምን እንደሚመስል በተጨባጭ ለማሳየት ያህል መንግስቱ ኃይለማሪያም ዝንብ እንኳን አልገደልኩም ብሎ መመፃደቁ አሳፋሪና የሚያሳዝን ሲሆን የኃይሌ ሥላሴ 54 ባለሥልጣኖች በሱ ብቸኛ ቀላጤ እንዲገደሉ ትዕዛዝ የሰጠበትን ደብዳቤና በግሌም የጓደኛ ክህደት ምን ያህል ዉስጣዊ ዕረፍት እንደሚነሳ አንባቢያን ይገነዘቡ ዘንድ፣ ዋቢ ሰነዶች ስካን በማድረግ እንዲቀርቡ አድርጌአለሁ፡፡ ኢትዮጵያችንን በሁለት እግር ማቋም ያልተቻለበትን ምክንያቶችና ዜጎች ስለወደቁበት የሚፅፉ ብዙ የመስኩ ሰዎች እንደሚኖሩ የታወቀ ቢሆንም፤ እኔም ከባህሩ ጬልፌ ልጨምርበትና አስተዋጽኦዬን ለማበርከት ስለአሰብኩ እንድትቀበሉኝ ከጉልበቴ ዝቅ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡

ሙሉውን መጽሐፍ ከታች ያንብቡ፡፡

Similar posts:

እውነት የኢትዮጵያ እምፓየር የመከላከያ ኃይል የሰላም አርበኛ ነው?

Baqala Garba's Departure Could Be A Potential Catalyst for Armed Struggle: Analyzing his Exit in the Context of the OFC's Letter

Harassment continued in Oromia| OLF-OLA Leaders Reveal Causes of Failure in Peace Deal

Paul Bernard Henze, a CIA Operative and Journalist's Advice to Meles to Destroy OLF